ሐይማኖታችንን እንወቅ ክፍል ሶስት።

በመሆኑም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተበደልኩት እኔ ነኝ የበደለኝ ሰው ነውና ሌላ ሶስተኛ ወገን ተገኝቶ እስኪያስታርቀን ድረስ ጥሉ ይቀጥላል ቢል ኖሮ እኛ ሰዎች ወድቀን መቅረታችን ነበር። እርሱ ግን የተበደለው እርሱ ሆኖ ሳለ  ራሱ ሰው ሆኖ የማስታረቁንም ስፍራ ወሰደ። እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስን ስናውቀው አንደኛ በሰው የተበደለና እርቅ የሚፈልግ አምላክ አድርገን ሁለተኛ ደግሞ ሰው የበደለውን በደል ከፍሎ ከርሱ ጋር የሚያስታርቀው ማንም ስለሌለ ራሱ ሰው በመሆን አስታራቂ ሆኖ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ እንዳስታረቀን አስታራቂ ማወቅ አለብን። ስለዚህ ታራቂ ስንል ተበዳይ ነውና ከሰው ልጆች ጋር መታረቅ አለበት አስታራቂ ስንል ደግሞ ያለ ልክ ወዶናልና እርሱ በተበደለ ራሱ ሊያስታርቅ የመጣ እንደሆነ መሆኑን ማወቅ አለብን። «በተበደለ ክሶ» እያሉ አበው የሚናገሩትም ለዚህ ነው። ስለዚህ  «ኢየሱስ ክርስቶስን ስታውቀው ወይም ታራቂ አለዚያ አስታራቂ ብቻ ብለህ ነው እንጂ አስታራቂ ማለት የለብህም» የሚለው አባባል ከወንጌሉ ውጭ ነው። እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊው ትምህርት ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው። አስታራቂም ታራቂም መካከለኛም መድረሻም ብሎ ማመን ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ የለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ ከተባለ ሰው ሁሉ በአንድ ወገን እግዘኢብሔር ደግሞ (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) በሌላኛው ወገን ሆነው ይታዩናል። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሰውነትን ገንዘቡ አድርጎ እኛን በማዳንና የዘላለም ሊቀ ካህናችን በመሆን መካከለኛ ሆኖአልና የሰው ዘር በሙሉ በርሱ መካከለኛነት ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኛል ይታረቃል። በርሱ መካከለኛነት ብቻ እግዚአብሔርን ያመልካል። እርሱ መለኮትንና ሰውነትን በተዋህዶ ስለያዘ ለዘላለም ሰውና እግዚአብሔር የተገናኙበት የማእዘን ራስ ነው። የማእዘን ራስ ድንጋይ ማለት ሁለት ወገኖችን አገናኝቶ የያዘ ማለት ነው። ስለዚህ ሚስጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ሲናገር « በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።፣» ይላል። (ኤፌ.2፡20-22) የማእዘን ራስ ነበረ አይደለም የሚለው አሁን የማእዘን ራስ ድንጋይ ነው። ለዘላለም ገንዘቡ አድርጎ የተዋሐደው ሰውነታችን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር አገናኝቶናል። ይህንን ታላቅ ሚስጢር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲተነትን

«ተምዐ እግዚአብሔር ላዕሌነ ሶበ አበስነ ሎቱ ወመጽአ ክርስቶስ ዓራቂ ማእከለ እግዚአብሔር ወዕጓለ እመሕያው ወዐረቆሙ ለክልኤሆሙ። (ኤፌ.2፡14 1ጢሞ.2፡5) መለኮትሰ ዘአቡሁ ወዘዚአሁ ወትስብእትሰ ዘዚአነ ወኮነ ዓራቄ ማእከለ ክልኤሆሙ ወአሠረ ክልኤተ ህላዌያተ በበይናቲሆሙ በተዋሕዶ ወከመዝ አማሰነ ቦቱ ጽልዓ»

 «እርሱን በበደልን ጊዜ እግዚአብሔር ፈርዶብን ነበር። እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስማማ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሁለቱንም አስታረቃቸው (ኤፌ.2፡14 1ጢሞ.2፡5) ይህንን ሲያብራራ እንዲህ በማለት ይቀጥላል «መለኮት የአባቱ ገንዘብ ነው የእርሱም ገንዘብ ነው ሥጋ ግን የእኛ ገንዘብ ነው። ሁለቱንም አንድ አደረገ ሁለቱን ባሕርያት እርስ በርሳቸው በተዋሕዶ አንድ አደረገ እንዲህ መለያየትንም አጠፋ።» (ሐይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ 68፡21-22)

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነትን ገንዘቡ አድርጎ ለዘላለም መዋሐዱና  በዚህ ተዋሕዶ በዙፋኑ መቀመጡ ቤተ ክርስቲያንን ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኘ መካከለኛ አደረገው።  ይህም ያለፈ ነገር ሳይሆን ለዘለዓለም የሚኖር እውነት ነው። የኛን ሰውነት በተዋሕዶ ለዘላለም ገንዘቡ ማድረጉ ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ኅብረትና ግንኙነት በዚህ ሰውነት መካከለኝነት እንዲሆን አደረገው። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛ ስንለው ምን ማለታችን እንደሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚገባ እያስተማረን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ ነው ማለት ሰዎች እንደሚያስቡት ጎንበስ ቀና እያለ ለኛ የሚጸልይ ማለት ሳይሆን በአንድ በኩል የኛን ሰውነት በሌላ በኩል የራሱና የአባቱ ገንዘብ የሆነውን መለኮት ይዞ ስላዋሐደና አንድ ስላደረገ እኛንና እግዚአብሔርን አገናኝቶናል ማለት ነው። ሁለቱን ባህርያት በተዋሕዶ አንድ አደረገ እንዲህ መለያየትን አጠፋ እያለን ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኝነት ይህ ነው። በመሆኑም ሌላ መለኮትንና ሰውነትን አዋህዶ የያዘ የለምና ከርሱ በቀር ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ መካከለኛ የለም። ይህም የተገኛንበት መካከለኛነት ለዛለለም ጸንቶ የሚኖር ነው። እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ወይም እኛን ምእመናን ይህን በሚመስል ድንቅና ከአዕምሮ በላይ በሆነ ክብር ነው ያከበረን ይለናል አሁንም ቅዱስ ዮሐንስ፡፡

 ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የኤፌሶንን መልእክት በተነተነበት ድርሳኑ  ስለዚህ ሚስጢር ሲናገር  «ወበእንተ ዝንቱ ይቤ ኩሎ አግረረ ሎቱ ታሕተ እገሪሁ ወኪያሁ ረሰየ ርእሰ ለቤተ ክርስቲያን ፈድፋደ እምነ ኲሎሙ ዘውእቱ ሥጋሁ ፍጻሜሁ ለኲሉ ፍጹም (ኤፌ.1፡19-23) ነጽር ኀበ ዓይ መካነ አዕረጋ ለቤተ ክርስቲያን ዘከመ ይእቲ ኲለንታሁ ሰሓባ በጥበብ እምሉዓሌ። ወከመዝ አዕረጋ ኀበ ልዕልና ዓቢይ ወለዝንቱ ዘውእቱ እምኔነ አንበሮ ዲበ ዝንቱ መንበር ወለነሂ ዓዲ ለቤተ ክርስቲያን ሰሐበነ እግዚአብሔር ኀቤሁ በከዊኖቱ ርእሰ ዚአነ እስመ ውስተ መካን ኀበ ሀሎ ርእስ ህየ ይሄሉ ሥጋ» (ሐይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 67፡38-40)

«ስለዚህም ሁሉን ከሥልጣኑ በታች አስገዛለት እርሱንም ከሁሉ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን ገዥዋ አደረገው ይኸውም በሥራ ፍጹም የሆነውን ሁሉ በክብር ፍጹም የሚያደርገው ሥጋውን ነው። እርስዋ አካሉ እንደመሆንዋ መጠን ቤተ ክርስቲያንን (ምእመናንን) ወደየትም ቦታ ከፍ ከፍ እንደ አደረጋት ዕወቅ ከልዕልና በጥበብ በጥበብ (በወልድ) ወደርሱ አቀረባት። እንዲሁም ወደ ደግ ክብር አወጣት ከኛ የተገኘውን ሥጋም በአምላክነቱ ዙፋን አስቀመጠው፡ እኛን ቤተ ክርስቲያንንም ገዥአችን በመሆኑ ወደ እርሱ አቀረበን፡ ራስ ካለበት ሕዋሳት ይኖራሉና። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የኛን ሥጋ ወስዶ ሰውነትን ገንዘቡ ካደረገ ጊዜ ጀምሮ ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙበት ብቸኛ መስመር ሆኖአል። ከዚህ ሌላ መገናኛ የለም። ቤተ ክርስቲያን ምስጋናና ጸሎትዋን ለእግዚአብሔር የምታቀርብበት መንገድም ይኸው እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያውጃል።

«እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥ ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።»  (ኤፌ.3፡20-21)

እንግዲህ በወንጌሉ ቃልና በአባቶቻችን በሐዋርያት በነቅዱስ ዮሐንስና በነቅዱስ አትናቴዎስ መንገድ ከሄድን መናፍቅ ማለት ይህንን እግዚአብሔር የኛን ባሕርይ ወስዶ ገንዘቡ በማድረግ በተዋሕዶ ወደ ራሱ እንድንቀርብ ያደረገበት ድንቅ መንገድ ትቶ ሌላ መንገድ የሚጠርግ ሰው ብቻ ነው። ሁላችንም ቤተ ክርስቲያናችን ያቆየችልንን ይህንን ሐይማኖተ አበው ገዝተን ብናነብ የጥንትዋን እና አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን ኦርቶዶክሳዊት እምነት በሚገባ ተረድተን እንይዛለን በርስዋም እንጓዛለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።