በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

«በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።»  (ኤፌ.4፡4-6)

ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት እርስዋም በጌታችንና በአምላካችን በመድኃኒታችንም በኢየሱስ ክቡር ደም የተመሠረተች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስትሆን ትምህርትዋና አካሄድዋም ስምዋ እንደሚያሳየው ቀጥ ያለችና የቀናች በተዋሕዶ ማለትም አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ብላ የኢየሱስ ክርስቶስን ሙሉ ማንነት ተቀብላ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑን የምታስተምር ናት። ተዋሕዶ የተባለችበት ምክንያት ብዙዎቹ ግማሾቹ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነቱን ክደው ሰው ብቻ ነው ሲሉ ግማሾቹ ደግሞ ሰውነቱን ዘንግተው አምላክ ብቻ ነው ሲሉ ቤተ ክርስቲያናችን ግን መለኮት ሥጋን ገንዘቡ በማድረጉ አምላክ ሰው ሆኖአል ሰው አምላክ ሆኖአል ብላ እውነተኛውን ወንጌል ይዛ በመቆምዋ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ሁለት ሺህ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ይህንን አስተምህሮ ይዛ ብትቆይም አሁን አሁን ግን ይህንን እውነት ክደው አባቶቻችን ያላስተማሩትን የሚያስተምሩ ታዋቂ አስተማሪዎች ተነስተው ይህንን ቤተ ክርስቲያናችን የተመሠረተችበትን እውነት የሚቃረን አስተምህሮ እያስተማሩ ነው። እነዚህም አስተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስና በሐይማኖተ አበው የተጻልንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሙሉ ማንነት ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑን የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት መሆኑን ፈጽሞ የሚክዱ ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ ሊቀ ካህናትም አስታራቂም ሊባል አይገባውም በማለት ህዝቡ አንዱን እንዲመርጥ እያስገደዱት ይገኛሉ።

ኢየሱስ ክርስቶስን አስታራቂ ነው ወይስ ታራቂ ነው? ሊቀ ካህን ነው ወይስ አምላክ ነው?  ብሎ አንድን ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ከነዚህ አንዱን ብቻ እንዲመርጥ ማስገደድ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን «ሰው ነው ወይም አምላክ ነው» ብለህ አንዱን ብቻ ምረጥ ብሎ እንደማስገደድም ነው። በእውነተኛው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትምህርት ሰው አንዱን መምረጥ የለበትም። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑን ማመን አለበት። ተዋሕዶ ማለትም ይህ ነው። አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ የምንለውም ለዚህ ነው። ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ማንነቱ ነው። ለዘላለም የኛን ማንነት ተዋሕዶአል። መለኮትንና ሰውነትን በተዋሕዶ ስለያዘ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ አስታራቂ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህን ተባለ። ስለዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ፣ ሊቀ ካህን፣ አስታራቂ ብለው ጠሩት። እርሱ ሁሉንም ነው። አምላክ ነው፣ ሰውነትን ገንዘብ አድርጎ በመዋሐዱም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው። ሊቀ ካህን ነው፣ አስታራቂ ነው፣ ታራቂም ነው።  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲናገር «ሶበ ትሰምዕ ስመ ክርስቶስ ኢተኃሊ ከመ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ባሕቲቱ አላ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ እንዘ አሐዱ ውእቱ» «ክርስቶስ ሲል ብትሰማ ብቻ አምላክ እንደሆነ ብቻ ሰውም እንደሆነ ብቻ አታስብ አንድ እንደ መሆኑ ሰው የሆነ አምላክ ነው እንጂ ።»  (ሐይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ 68፡40)

አስታራቂ ነው ስንል ታራቂነቱን እየረሳን አይደለም። ገንዘቡ ባደረገው ሰውነታችን በመስቀል ላይ ሞቶ ቢያስታርቀንም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ በሆነበት መለኮትነቱ ደግሞ ታራቂያችን ነው። አስታራቂም ታራቂም ነው። ሰውነትና መለኮት ተዋሕዶ አንድ ሆነ ስንል ታራቂና አስታራቂ አንድ ሆነ ማለታችን ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ነው ስንል ሊቀ ካህንነቱን እየረሳን አይደለም። ሊቀ ካህን ነው ስንልም አምላክነቱን ይዞ ነው ሊቀ ካህን፣ አስታራቂ፣ መካከለኛ የተባለው። ይህ የመዳናችን ሚስጢር ነው። ይህ የኦርቶዶክስ ሐይማኖታችን ሚስጢር ነው። አባቶቻችን ሐዋርያት ከዚያም ቀጥሎ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ እነ ቅዱስ ቄርሎስ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሐይማኖተ አበው ጽፈው ያስተላለፉልን እውነት ይህ ነው።  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህንና አስታራቂ፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ ነው የሚል ሁሉ መናፍቅ ሊባል አይገባም።  ይህ አምላክነቱን መካድ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ ሲጠማ፣ ሲራብ፣ በመስቀል ላይ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ ሲል፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ሲማልድልንም አምላክነቱን እንደያዘ እንጂ አምላክነቱን ትቶ አልነበረም። መቼም ቢሆን ለቅጽበተ ዓይንም ቢሆን ከአምላክነቱ አልጎደለም።

«እንዘ አምላክ ውእቱ ናሁ ኮነ ሰብአ ወኢወጽአ ግሙራ እምስብሓተ መለኮቱ ወለእመኒ ኮነ ውስተ ከፍል እምነ ፍጡራን ውእቱሰ ይትሌዐል ላዕለ ኩሉ ፍጥረታት እንዘ ሐጋጌ ሕግ በመለኮቱ ናሁ ኮነ መትሕተ ሕግ ወነበረ በዘቦቱ እንዘ ይሔግግ ሕገ  እንዘ እግዚእ ውእቱ በመለኮቱ ናሁ ነስአ አርአያ ገብር ወኢተአተተ እምኔሁ ሥርዓተ እግዚእና እንዘ ዋሕድ ውእቱ ናሁ ኮነ በኩረ ለብዙኃን አኀው ወነበረ በተዋሕዶቱ።»

«አምላክ ሲሆን ሰው ሆነ ከጌትነቱም ክብር ፈጽሞ  አልተለየም ምንም ሰው ቢሆን እርሱ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ነው።  በመለኮቱ ሕግን የሠራ ሲሆን እንሆ ሕግን በመፈጸም ተገኘ ሕግን  ሲሰጥ በነበረበት ባሕርዩ ጸንቶ ኖረ (ገላ.4፡4) በመለኮቱ ገዢ ሲሆን የተገዢ ባህርይን ገንዘብ አደረገ ግን የጌትነት ክብር ከርሱ አልተለየም። (ሐይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ 70፡4-5)

«ሐመ ወጥዕመ ሞተ በሥጋ በፈቃዱ በዲበ መስቀል እንዘ አሐዱ ውእቱ ምስለ ሥጋ ዘቦቱ ጥዕመ ሞተ ወቦቱ ፈጸመ ዘንተ ሥርዓተ ከመ ዘሎቱ አሐዱ ህላዌ መለኮት ምስለ ሥጋ እምአመ ኀደረ ውስተ ከርሥ»

«ታመመ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ጋር አንድ ሆኖ በመስቀል ላይ በፈቃዱ በሥጋ ሞተ አንድ ባህርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማህጸን ካደረ ዠምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይህንን ሥርዓት ፈጸመ» (ፊሊ.2፡5-9) ሐይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ 70፡28