ሐይማኖታችንን እንወቅ ክፍል ሁለት።

ከዘላለም እስከ ዘለዓለም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ አምላክ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት ካረገም በኋላ ዘላለማዊ ሊቀ ካህን ለሰው ልጆች የሚራራ መካከለኛ እያለ ሲጠራው ከአምላክነቱ ለይቶት ሳይሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት አምላክ ሆኖ ሳለ ነው ይህንን ሁሉ የሆነው። ዛሬ ከእውነተኛው የኦርቶዶክስ ትምህርት የተለዩና ይህንን የጥንት አባቶቻችን በሐይማኖተ አበው ያስተላለፉልንን እውነት የሚክዱ አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያናችን ተነስተዋል። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ እንደሚገባ የሚያውቁት ሊቃውንት ግማሾቹ ሰሚ አጥተው ግማሾቹ ሐሰተኞቹን የሚከተል ህዝብ ስለበዛ ፈርተው ዝም ብለዋል። ሐይማኖተ አበውና ሌሎችም የቤተ ክርስቲያናችን ዋና መጻሕፍት ግን ለሚያነባቸው ይናገራሉ። ህዝቡ ግን የቤተ ክርስቲያኑን መጻሕፍት ማንበብና እውነተኞቹን ሊቃውንት አባቶች መስማት ትቶ በአቋራጭ ራሳቸውን ዙፋን ላይ ያወጡትን ያልተማሩ አፈኞች እየሰማ ስለሆነ ከቤተ ክርስቲያንዋ አስተምህሮ እየራቀ ነው። ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን  ከሐዋርያትና ከሰለስቱ ምእት ተቀብላ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት ያቆየቻቸውን ትምህርቶች ዛሬ እየተቃወሙአቸው ለሌሎች ቤተ እምነቶች እየሰጡአቸው ያሉት። እነዚህ ያልተማሩ አፈኞች የእብራውያንን መልእክትና በአጠቃላይ የሐዋርያው ጳውሎስን መልእክቶች ክደው የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትና በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ የመሆኑ ነገር ኢየሱስ በምድር ላይ እያለ ብቻ የሰራና ያለፈ  ነው፣አሁን ግን አምላክ ብቻ ሆኖ በክብሩ ተቀምጦአል። አሁን መካከለኞችና አማላጆች ሌሎች ቅዱሳን ናቸው እያሉ ህዝቡን እያሳቱት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ ነው ሊቀ ካህናት፣ መካከለኛ አስታራቂ እያለ የሚጠራው። ለምሳሌ በጢሞቴዎስ መልእክት ላይ ያለውን እንመልከት «አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤» (1.ጢሞ.2፡5) በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ ነው የሚለው እንጂ ነበረ አይደለም የሚለው። ይህን የሚጽፈው ጌታችን ካረገ በኋላ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገም በኋላ ሰውነትን ገንዘብ አድርጎ ለዘላለም ስለተዋሐደና የዘላለም ሊቀ ካህን ስለሆነ እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ የሚያየውና የሚያውቀው በርሱ ነው። ለዚህም ነው በእብራውያን  መልእክት ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር «ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን።» ( እብ.2፡9) ሞትን መቅመሱን ከሞት መከራ የተነሳ ከመላእክት ማነሱን ያለፈ ታሪክ አድርጎ ያስቀምጥና አሁን ግን የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጮኖ እናየዋለን ይለናል። በሶስተኛው ምእራፍ ላይም የሐይማኖታችን ሊቀ ካህናት እርሱ ነውና ተመልከቱት ይላል። «ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤» ( እብ.3፡1) አሁን ተመልከቱ እያለን ነው። የሐይማኖታችን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሞትን አሸንፎ ከሙታን ተነስቶ አሁን የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጮኖ በዙፋኑ አለ ይለናል። የሐይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ ሲል እግዚአብሔርነቱን ረስቶ ነው? በጭራሽ። አምላክነቱንማ በመጀመሪያው ምእራፍ ላይ እንዲህ በማለት አስረግጦ አስቀምጦልናል ««ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ (ዕብ.1፡1-3) «ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል። ስለ መላእክትም፦ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።» (ቁ.6-8) «ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።» (ቁ.10-12) ስለዚህ ሐዋርያው አምላክነቱን በሚገባ ካሳየን በኋላ ነው ይህ አምላክ የኛን ሰውነት ገንዘብ በማድረጉ የዘላለም ሊቀ ካህናችንም ሆኖአል የሚለን። አሁን በዚህ ዘመን የተነሱት ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑት አስተማሪዎች ግን አሁን አምላክነቱን ብቻ ወይም አምላክ መሆኑን ብቻ ነው ማየት ያለብን ይሉናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግን በክህነቱ ተመልከቱት እያለን ነው።  እንደመልከጸዴቅ ክህነት የዘላለም ካህን ስለሆነ አሁንም እስከዘላለምም ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡት በርሱ ሊቀ ክህንነት ነው። ይህ ማለት ግን ከአብና ከመንፈስ ቅደስ ያነሰ ነው ማለት አይደለም። ግን ሰውነታችንን ገንዘብ አድርጎ ስለተዋሐደ አሁንም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው። ስለዚህ ሰውን አንዱን ምረጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ወይ አምላክ ብቻ ወይ ሰው ብቻ ወይ ታራቂ ብቻ ወይ አስታራቂ ብቻ በል ማለት መናፍቅነት ነው። ምክንያቱም እርሱ በተዋህዶ አምላክም ሰውም ነውና። ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር ያለ መካከለኛ ነው አስታራቂ ነው የሚለውን የአባቶቻችንን የሐዋርያትን ወንጌል ስንሰብክ እርሱ አምላክ ከሆነ ወደ ማን ያስታርቀናል? የሚል ተልካሻ ምክንያት በመስጠት ህዝቡን ሲያደናግሩ ይታያሉ። እንዲያውም ሊቀ ጥበብት፣ ሊቀ ስልጣናት የሚባል አባቶቻችን ሐዋርያት የማያውቁት የማእረግ ስም የያዙ አንዳንዶች « ሰው ሁሉ የሚያውቀውን አማርኛ የኢትዮጵያ የቋንቋ ጥናት መሥሪያ ቤትን እንኳ ሳያማክሩና ሳያስፈቅዱ ዓይኔን ግንባር ያርገው ብለው ማለደ ማለት ፈረደ ማለት ነው ብለው በአደባባይ ሲናገሩ ሰምተናል። ስንቱን አማርኛ ቀይረው ይችሉት ይሆን? አሁን የሚያስፈራው አባቶቻችን ለሁለት ሺህ ዓመታት  ጠብቀው ያቆዩልንን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ እንዳይቀይሩት ወይም የሐዋርያው የጳውሎስን መልእክቶች ቀደው እንዳያወጡአቸው ብቻ ነው።  ቃሉ እንደሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፣ የአዲስ ኪዳንም ሊቀ ካህን ነው፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ ነው  የሚሉትን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የካዱ በማስመሰል ህዝቡ ይህንን የአባቶቹንና የራሱ የሆነውን እውነተኛ ትምህርት እንዳይሰማ ይጥራሉ። እውነታው ግን አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ አስታራቂ ነው መካከለኛ ነው። በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ የአዲስ ኪደን አስታራቂ እርሱ ነው የሚለው እውነተኛ ወንጌል ሲነገር አምላክ ከሆነ ወደ ማን ያስታርቃል? በማለት ለሚጠይቁ  በራሳቸው ጥያቄ እነርሱን ልጠይቃቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ አምላክ አልነበረም? አምላክ ከሆነ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው እያለ ደሙን በማፍሰስ ያስታረቀን ከማን ጋር ነበር? ከእግዚአብሔር ጋር እንደምትሉ እርግጠኛ ልሁንና ጥያቄየን ልቀጥል አምላክ ከሆነ ከማን ጋር ነው ያስታረቀን? ብየ የራሳችሁን ጥያቄ ልጠይቃችሁ። የሚያስታርቅ ሁሉ አምላክ አይደለም ካላችሁ እንግዲያው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ሲያስታርቀን አምላክ አልነበረም ማለት ነዋ? ይህን እንዳትሉ ቃሉ ይከለክላችኋል ። እርሱስ ለዘላለም አምላክ ነው። ግን ሁላችንም በአዳም ምክንያት ኃጢአተኞች ስለሆንንና ሌላ አስታራቂ ስለሌለን ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሰረት ራሱ ተበድሎ ራሱ ሊክስ  ጠላቶቹ የሆንነውን በመስቀል ሞቱ ራሱ ሊያስታርቀን ሰው ሆኖ መጣና ታራቂው አስታራቂም ሆነ። አዎ በሰው አስተሳሰብ ካየነው ሁለት ሰዎች ከተጣሉ ሁለቱም ታራቂዎች እንጂ አስታራቂዎች መሆን አይችሉም። ሁለቱም እርስ በርስ ተጣልተዋልና ከሁለቱም ጋር ያልተጣላና የሁለቱም ወዳጅ የሆነ ሰው ካልተገኘ መታረቅ አይችሉም። በኛ በሰዎች ዘንድ የተለመደው ይህ ነው። በእኛ በሰው ልጆች እና በእግዚአብሔር መካከል የሆነው ግን ከዚህ የተለየ ነው። በአዳም ምክንያት ሰው ሁሉ ስለሞተና ኃጢአተኛ ስለሆነ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ ሆኖ ሊያስታርቀን የሚችል አልነበረም። ቢኖር ኖሮ አምላክ ከሰማይ ወርዶ ሰው መሆንም ባላስፈለገው ነበር። ለዚህም ነው አዳም በወደቀ ጊዜ እግዚአብሔር በእከሌ እንታረቃለን ወይም እከሌ ያስታርቀናል የሚል ተስፋ ያልሰጠው። ነገር ግን ራሱ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ የእባቡን ራስ በቀራንዮ መስቀል ላይ በመቀጥቀጥ እንደሚያድነን ተስፋን ሰጠው። (ዘፍ.3፡15)  ከዚህ ውጭ ግን ሌላ ሶስተኛ ወገን የሆነ አስታራቂ አልነበረም። እንዲያውም ነቢዩ ኢሳይያስ ሲናገር «እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል። እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ፡፡ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ።» ይላል። (ኢሳ.59፡15-17) አዎ እግዚአብሔር እርሱንና ሰውን ሊያስታርቅ የሚችል ማንም እንደሌለ አይቶአልና ራሱ የበቀልን ልብስ ለበሰ። በለበሰው ሥጋ በመስቀሉ ላይ ጠላታችንን በመበቀል ከዘላለም ሞት አዳነን። ይህን ታላቀ ሚስጢር ቅዱሳን አባቶቻችን እንዲህ ያስተምሩናል። እንስማቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በሐይማኖተ አበው ላይ ሲናገር

«እስመ ለሊሁ ነጸረነ ወናሁ ኮነ አጽራረ ለእግዚአብሔር ወአልብነ ምንትኒ ግሙራ ዘይክል ያቅርበነ ኀቤሁ ለዐቂበ ሀብቱ ኢኪዳን ወኢመስዋእት ወበእንተ ዝንቱ ተሣሃለነ ወኢያንሥአ ለነ ሊቀ ካህናት እመላእክት ወኢእምኃይላት እለ እሙንቱ ይቀውሙ ዐውደ መንበሩ አላ አሐዱ ለሊሁ ወረደ ወተሠገወ እምህላዌነ ወኮነነ ሊቀ ካህናት ወአዕረገ በእንቲአነ ሥጋሁ መሥዋእተ ለአቡሁ ወአብጽሐነ ሎቱ በዘቦቱ ሐመ» (እብ.9፡28)

«እርሱ ተመልክቶን እንሆ ለእግዚአብሔር ጠላቶቹ ሆነን ተገኘን፡ ሀብቱን ለማግኘት ኪዳንም ቢሆን መስዋዕትም ቢሆን ወደ እርሱ ያቀርበን ዘንድ የሚችል ፈጽሞ አልነበረንም። ስለዚህ ይቅር አለን ዙፋኑን ከበው ከሚቆሙ ከመላእክት ከኃይላትም  ወገን ሊቀ ካህናት አልሾመልንም እርሱ አንዱ ወደዚህ ዓለም  ወርዶ ባሕርያችንን ባሕርይ አድርጎ ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) ሆነን እንጂ ስለእኛም ሥጋውን መስዋእት አድርጎ ወደ አባቱ አቀረበ እንጂ በታመመበት በሥጋው ለርሱ ገንዘብ ለመሆን አበቃን (እብ. 9፡28) ሐይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ 62፡15-16)